Skip to main content

ሁለንተናዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶች 

ያለአንዳች መዘናጋት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ፦

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

ሆሳዕና ፣ሰኔ 22 ፣2018፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር 

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ በልዩ ትኩረት እየተመሩ የሚገኙ ተግባራትን 

ወቅታዊ የአፈጻጸም ደረጃ በበይነ መረብ አማካይነት ዛሬ ገምግመዋል፤ 

ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል።

የአፈጻጸም ግምገማው በፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ፣ በመሶብ - የአንድ 

ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ዝግጅት ፣በኢትዮ - ኮደርስ ስልጠና፣ 

በገቢ አሰባሰብ ፣በከተማና በገጠር ኮሪደር ልማት ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ 

ስራዎች አፈጻጸም፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ኑሮ ውድነትትን 

ማረጋጋት በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑ ተመልክቷል።

የተግባራቱን ወቅታዊ አፈጻጸም ደረጃ የተመለከተ ሪፖርት በሚመለከታቸው 

ቢሮዎች ኃላፊዎች በኩል ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለፁት ፤ 

ሁለንተናዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶች ያለአንዳች 

መዘናጋት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።


እየተጠናቀቀ በሚገኘው በጀት ዓመት ቀሪ ጊዜያትም ይሁን በመጪው አዲሱ በጀት ዓመት ፣ 

በሁሉም መስኮች የህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የየደረጃው አመራር በትጋት 

መንቀሳቀስ የሚጠበቅበት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) 

አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል ።

በሁለተኛው ዙር መሶብ - የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንቅስቃሴ የወራቤ፣ የወልቂጤ፣ 

የሆሳዕና ፣ የሀላባ ቁሊቶ እና የዱራሜ ከተሞች ማዕከላት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት 

ክፍት መሆናቸው በመደረኩ የተጠቀሰ ሲሆን ፣የቡታጅራ ከተማ ማዕከልም ከጥቂት 

ቀናት በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል። 


ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ማዕከላት ወደተሟላ መንግስታዊ አገልግሎት 

መስጠት ስለመግባታቸዉ በየመቅሩ የቅርብ ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል ።
ከፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ አንፃር እስከ ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓመተ ምህረት ድረስ ባለው 

ጊዜ በክልሉ ከ3 ሚሊየን 1መቶ ሺህ በላይ ያህል ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ መውሰዳቸው 

በመድረኩ ተገልጿል ።

የኢትዮ - ኮደርስ ስልጠናውም ተጠናክሮ መቀጠሉ በውይይቱ የተዳሰሰ ሲሆን፣ 

ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ አጠናቅቀው ሰርተፍኬት የሚወስዱበት ሁኔታ በትኩረት 

እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከገቢ አሰባሰብ አንፃር እስከ ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓመተ ምህረት ድረስ 24 ነጥብ 7 

ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተጠቀሰ ሲሆን፣ይህም በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ 

ከታቀደው 27 ቢሊየን ብር ዕቅድ አንፃር አፈጻጸሙ 91 ነጥብ 5 በመቶ መደረሱን 

ያመለክታል ተብሏል ።

በከተማ እና በገጠር ኮሪደር ልማት ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ስራዎች አፈጻጸም፣ የክረምት 

በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ኑሮ ውድነትትን ማረጋጋትን በተመለከቱ ጉዳዮች ወቅታዊ 

አፈፃፀም ሁኔታ ዙሪያ ዝርዝር ውይይት ተደርጓል ፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።

በመድረኩ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር 

ዲላሞ ኦቶሬን ጨምሮ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣ የክልሉ ካብኔ አባላት፣ 

የዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ዋና አስተዳዳሪዎች እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም 

ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

Image