በሪፎርም እሳቤ እና በመደመር መንገድ የጀመርናቸው ስራዎች ውጤት
እያስመዘገቡ ነው ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )
ሆሳዕና፣ነሐሴ 21/2018 ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት እና
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 2ኛ ዙር የጋራ የምክክር ፎረም በሆሳዕና
ከተማ መካሄድ ጀምሯል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )
የምክክር ፎረሙን በከፈቱበት ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት
በሪፎርም እሳቤ እና በመደመር መንገድ የጀመርናቸው ስራዎች ውጤት
እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአይነቱ ልዩ የሆነ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ለ46 ቀናት ከ4ሺ
በላይ ተመካካሪዎች ከ400 በላይ ጉዳዮችን አንስተው ከ99 በመቶ በላይ
በመግባባት በጥቂት ጉዳዮች ደግሞ የጋራ መግባባት እንዲፈጠርባቸው
መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል።
በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ለመንግስት ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ የጋራ መግባባት
በመፈጠሩ ኢትዮጵያ ተወያይታለች:- ኢትዮጵያ ተስማምታለት፣አሸንፋለች
ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የጀመረቻቸውን ስራዎች ለማጠናከር፣የህዝቡን
ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እያረጋገጠች ትገኛለች ብለዋል።
በሁሉም መስክ የጀመርነው ጉዞ ትክክለኛ መሆኑን በተለያየ መንገድ ማረጋገጥ
ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ላይ
የተሳተፈው ህዝባችን ለጀመርነው ስራ እውቅና ሰጥቷል።
ለወደፊትም የጀመርናቸው ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዲችሉ ህዝቡ
ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ማረጋገጡን ርዕሰ መስተዳድሩ
አስረድተዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በክልሉ በሁሉም ስራዎች ያላቸው ተሳትፎ
ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።
በክልሉ በትምህርት፣በጤና፣በውሃ በተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ላይ
ያላቸው ተሳትፎ ጉድለትን በመሙላት ብቻ ሳይሆን ለተጀመረው የቤተሰብ
ብልጽግና አቅም ሆነው ስለመታየታቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ በአብነት ጠቅሰዋል።
የአንድ ሀገር እና ክልል እድገት የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት
ርዕሰ መስተዳድሩ የተገኘውን ሀብት በቁጠባ እና በተቀናጀ መልኩ መጠቀም ደግሞ
ውጤቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል።
በታሪክ ውስጥ የተቋም እና የሀገር ግንባታ አካል መሆን ያኮራል ያሉት ርዕሰ
መስተዳድሩ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምትመች ሰላሟ የተረጋገጠ፣ዘላቂ ልማት ያላት፣
የተግባባ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የሁላችንም ስነ ልቦና በሰላም እና በልማት ላይ መገንባት ይኖርበታል ሲሉም
ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ሀገሩን የሚወድ፣የሀገሩን ጥቅም የሚጠብቅ ትውልድ በመገንባት የዘመኑ አርበኛ
መሆን ይጠበቃል ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዚህ አመት በሚኖራቸው ስራዎች የተለመደውን
ሀላፊነት በላቀ ደረጃ መወጣት እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።