admin
ቲዩ, 01/28/2025 - 16:40
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ከከምባታ ሰጄ ጎቾ የባህል ሽማግሌዎች ጋር በአብሮነት፣ በሰላምና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በዱራሜ ከተማ ውይይት አካሔዱ
ሆሳዕና፣ጥር 17/2017 ፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ከከምባታ ሰጄ ጎቾ የባህል ሽማግሌዎች ጋር በአብሮነት፣ በሰላምና በልማት ጉዳዮች ያተኮረ ውይይት አካሒደዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከባህል ሽማግሌዎቹ ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ እንደገለጹት፣ በክልሉ ልማት ላይ የከምባታ ህዝብ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።
በዞኑ እየተስተዋለ ያለውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት ረገድ የሀገር ሽማግሌዎቹ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው አመላክተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በዞኑ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ በቅንጅት እና በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎት ልማት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአመራሩ እና በህዝቡ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ፍላጎት ያላቸው አካላትን ሴራ ወደ ጎን በመተው ለላቀ ውጤት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የከምባታ ሰጄ ጎቾ የሀገር ሽማግሌዎች በውይይት መድረኩ እንደገለጹት በትምህርት፣በጤና፣በንጹህ መጠጥ ውሃ፣በመንገድ እና በሌሎችም ዘርፎች የተስተዋሉ የልማት ውስንነቶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮች ለዞኑ ልማት እንቅፋት መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎቹ ጠቁመዋል።
የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በአመራሩ መካከል ከፋፋይ አጀንዳ በመፍጠር በዞኑ ልማት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገሩት የሀገር ሽማግሌዎቹ የዞኑን እድገት የማይፈልጉ አካላትን እኩይ ተግባር በጽናት እንደሚታገሉ ጠቁመዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የከምባታን የሀገር ሽማግሌዎች ጥያቄ በክብር ተቀብለው በዞኑ የተስተዋለው ችግር እንዲፈታ የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው የሀገር ሽማግሌዎቹ ምስጋና አቅርበዋል።
ለዞኑ ልማት እና እድገት አመራሩ እና ህዝቡ ተቀናጅተው ለመስራት በመድረኩ ከስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።
በመድረኩ የከምባታ ዞን ተወላጅ የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ከከምባታ ዞን፣ከወረዳዎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ የተውጣጡ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
Image
