አዲሱ 2019 _ በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በክልሉ የጀመርናቸው
የልማት ስራዎች የሚሳኩበት ብሩህ ጊዜ ነው:- ርዕሰ መስተዳድር
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር
ሆሳዕና፣መስከረም 12/2019)ለ 'ያሆዴ '_የሀዲያ ብሔር ዘመን
መለወጫ በዓል በሀዲይ ነፈራ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ለበዓሉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ያሆዴ በዓል
ከረጅም ድካምና ልፋት በኋላ መላው ማህበረሰባችን በጉጉት የሚጠብቀው
እና ህብረተሰቡ በጋራ ተገናኝቶ ዘመድ የሚጠይቅበት ሌሎች መልካም
እሴቶቻችን ጎልተው የሚታዩበት ነው ብለዋል።
የመስከረም ወር ለክልሉ ማህበረሰብ የደስታ ጊዜ ነው ያሉት ርዕሰ
መስተዳድሩ በተለይም ለሀዲያ ብሔረሰብ የተለየ ስለመሆኑም
አመላክተዋል።
የክረምቱ ወቅት ጨለማ አሊያም ጭጋግ ሳይሆን ይህ ጊዜ ፈጣሪ
ያስቀመጠው ውብ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል።
ክረምትን፣በጋን፣ጸደይን ብሎም በልግን ለሰጠን ፈጣሪ ምስጋና ይገባል
ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ያሆዴ በዓልን ስናከብር ስለ ሀገራችን ሰላም አንድነት፣ስለ ህዝቦች መፈቃቀር
ስለመከባበር፣የሰላም እና የልማት ጉዳዮችን አጣምረን ነው ብለዋል።
ያሆዴን በአል ከዚህም በላይ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀት ይኖርብናል
ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በአሉን ተሰባስበን
ያከበርንበት ሁኔታ የተለየ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
ከሀገር ውጪ ያሉ ተወላጆች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በዓሉን ሲያከብሩ ስለ
ልማት፣ስለ ሰላም፣ስለ ቤተሰብ ስለ ባህላችን የሚመካከሩበትን እድል
እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
2019 ዓ/ም ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ብዙ ችግሮቻችንን
የምንሻገርበት፣በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በክልሉ የጀመርናቸው የልማት ስራዎች
የሚሳኩበት ስለመሆኑም አመላክተዋል።
ዓመቱ የህዝባችንን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የምናሳድግበት ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ እንዲሳካ በገንዘብ በሙያ በእውቀት እና በልዩ ልዩ መስክ ተሳትፎ
ላደረጉ አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል።
ያሆዴ የሰላም የፍቅር፣ህዝብን የማገልገል እና የይቅርታ በዓል እንዲሆን
ርዕሰ መስተዳድሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።