admin
Thu, 05/01/2025 - 19:25
ርዕሰ መሰተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ ( ዶ/ር) 1ሺ 446ኛዉን የዒድ አልፈጥር በዓልን አሰመልክተዉ ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፤ የመልዕክታቸዉም ሙሉ ቃል የሚከተለው ነዉ፤
ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺ 446ኛዉ የዒድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሃይማኖታዊ ትርጉምና ሥፍራ በሚሰጠዉ በረመዳን ወር የሚከናወኑ መልካም ተግባራት በፈጣሪ / በአላህ/ ዘንድ ከፍ ያለ ምንዳን የሚያስገኙ ከመሆናቸዉም በላይ ለወንድማማችነትና ለእህትማማችነት እሴቶች ማበብ ጉልህ ሚና አላቸዉ ፣ የረመዳን ወር የመተዛዘን፣ የመረዳዳትና የመተባበር ተግባራት የሚጠናከሩበት፣ በአጠቃላይ የመልካምነት መንፈስ ከፍ ብሎ የሚንፀባረቅበት ነዉ።
በረመዳኑ ወር ሲከናወኑ የነበሩ ልዩ ልዩ የጋራ የኢፍጣር ስነ ስርዓቶች ፣ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሌሎች እምነቶች ተከታይ ከሆኑ እህት ወንድሞቹ ጋር ማዕድ የተቋደሰባቸዉ፣ ብዝሃነትን ማጎልበቻ የአብሮነት እሴቶችን ማፅኛ፣ ከመሆናቸውም ባሻገር ፣ የመቻቻልና የመከባበር መንፈስን ማጠናከሪያ ናቸዉ፤ የወል እሴቶችን መሠረት ያደረገ፣ የጋራ ትርክት ለመገንባትም የበኩላቸዉን አዎንታዊ ሚና ያበረክታሉ ። የኢፍጣር መረሐ ግብሮች በአንዳንድ የክልላችንና የሀገራችን ክፍሎች በተለያዩ መነሻዎች የተከሰቱ የእርሰ በርስ አለመግባባቶችን ተቀራርቦ በመፍታት ፣ እርቅና ሠላም ለማዉረድ፣ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማደስ ምቹ አጋጣሚና ዕድል እየፈጠሩ ናቸዉ ።
ስለሆነም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳኑ ወር ሲያዘዉትራቸዉ የነበሩ መልካም ተግባራትን በማስቀጠል፣ ለአብሮነት እሴቶች መፅናት ፣ለዘላቂ ሠላም እዉን መሆን፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለጋራ ልማት መፋጠን ከወትሮዉ በላቀ ትጋት እንዲንቀሳቀስ ጥሪዬን አቀርባለሁ ፣
በዓሉ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተባበር መንፈስን ማደሻ እንዲሆን እመኛለሁ ።
ዒድ አልፈጥር ሙባረክ!
Image
